Deuteronomy 19

መማጸኛ ከተሞች

19፥1-14 ተጓ ምብ – ዘኍ 35፥6-34፤ ዘዳ 4፥41-43፤ ኢያ 20፥1-9 1አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ምድራቸውን ለአንተ የሚሰጥባቸውን አሕዛብ በሚደመስሳቸው ጊዜና አንተም እነርሱን አስለቅቀህ በከተሞቻቸውና በቤቶቻቸው በምትቀመጥበት ጊዜ፣ 2አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር አማካይ ስፍራ፣ ሦስት ከተሞችን ለራስህ ለይ። 3ሰው የገደለ ሁሉ እንዲሸሽባቸው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር መንገዶችን ሠርተህ፣ በሦስት ክፈላቸው።

4በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ገድሎ ሕይወቱን ለማትረፍ ለሚሸሽ ሰው መመሪያው የሚከተለው ነው። 5እነሆ፤ አንድ ሰው ከባልንጀራው ጋር ዕንጨት ለመቍረጥ ወደ ጫካ ቢሄድ፣ ዛፉን ለመጣል መጥረቢያውን በሚሰነዝርበት ጊዜ ብረቱ ከእጀታው ወልቆ ባልንጀራውን በመምታት ቢገድለው፣ ያ ሰው ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ ሕይወቱን ማትረፍ ይችላል። 6አለዚያ በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ቢገድል፣ መንገዱ ረዥም ከሆነ ደም ተበቃዩ በንዴት ተከታትሎ ይደርስበትና መገደል የማይገባውን ሰው ሊገድል ይችላል። 7ሦስት ከተሞችን ለራስህ እንድትለይ ያዘዝሁህ በዚሁ ምክንያት ነው።

8ለአባቶችህ በመሐላ በገባላቸው ቃል መሠረት፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወሰንህን ሲያሰፋውና ለእነርሱ በሰጣቸው መሠረት ምድሪቷን ሁሉ ሲሰጥህ፣ 9አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትወድድና ምንጊዜም በመንገዱ እንድትሄድ ዛሬ የማዝዝህን እነዚህን ሕግጋት ሁሉ በጥንቃቄ የምትጠብቅ ከሆነ፣ በእነዚህ ላይ ሌሎች ሦስት ከተሞችን ትጨምራለህ። 10አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር የንጹሕ ሰው ደም እንዳይፈስስና በሚፈስሰውም ደም በደለኛ እንዳትሆን ይህን አድርግ።

11ይሁን እንጂ አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢጠላው፣ አድፍጦ ጥቃት ቢያደርስበት፣ ቢገድለውና ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ቢሸሽ፣ 12የሚኖርባት ከተማ ሽማግሌዎች ሰው ልከው ከከተማው ያስመጡት፤ እንዲገድለውም ለደም ተበቃዩ አሳልፈው ይስጡት።

13አትራራለት፤ ነገር ግን መልካም እንዲሆንልህ የንጹሑን ደም በደል ከእስራኤል አስወግድ።

14አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ውስጥ ለአንተ በሚተላለፍልህ ርስት ላይ የቀድሞ ሰዎች ያስቀመጡትን የባልንጀራህን የድንበር ምልክት አታንሣ።

ምስክሮች

15በማንኛውም ወንጀል ወይም ሕግ በመተላለፍ ሰውን ጥፋተኛ ለማድረግ፣ አንድ ምስክር አይበቃም፤ ጕዳዩ በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ምስክርነት መረጋገጥ አለበት።

16ተንኰለኛ የሆነ ምስክር አንድን ሰው በሐሰት ቢከስስ፣ 17ክርክሩ የሚመለከታቸው ሁለቱ ሰዎች በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት፣ በዚያ ወቅት በሚያገለግሉት ካህናትና ፈራጆች ፊት ይቁሙ። 18ፈራጆችም ጕዳዩን በጥልቅ ይመርምሩት፤ ያም ምስክር በወንድሙ ላይ በሐሰት የመሰከረ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ 19በወንድሙ ላይ ለማድረግ ያሰበውን በእርሱ ላይ አድርጉበት፤ ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ። 20የቀሩትም ሰዎች ይህን ሰምተው ይፈራሉ፤ እንዲህ ያለው ክፉ ነገርም ለወደፊቱ በመካከልህ ከቶ አይደገምም። 21ርኅራኄ አታድርግ፤ ሕይወት በሕይወት፣ ዐይን በዐይን፣ ጥርስ በጥርስ፣ እጅ በእጅ፣ እግር በእግር ይመለስ።

Copyright information for AmhNASV